Psalms 10

ለፍትሕ የቀረበ ልመና

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምን እንዲህ ርቀህ ቆምህ?
በመከራ ጊዜስ ለምን ድምፅህን አጠፋህ?

2ክፉዎች የተጨነቀውን በእብሪት ያሳድዳሉ፤
በወጠኑት ተንኰል ይጠመዱ።
3ክፉ ሰው በልቡ ምኞት ይኵራራል፤
ስግብግቡን ይባርካል፤ እግዚአብሔርንም ይዳፈራል።
4ክፉ ሰው ከትዕቢቱ የተነሣ እግዚአብሔርን አይፈልግም፤
በሐሳቡም ሁሉ አምላክ የለም፤
5መንገዱ ዘወትር የተሳካ ነው፤
ዕቡይ፣ ከሕግህም የራቀ ነው።
በመሆኑም በጠላቶቹ ላይ ያፌዛል።
6በልቡም፣ “ከስፍራዬ የሚነቀንቀኝ የለም፤
ከትውልድ እስከ ትውልድም መከራ አያገኘኝም” ይላል።

7አፉ መርገምን፣ ቅጥፈትንና ግፍን የተሞላ ነው፤
ሽንገላና ክፋት ከምላሱ ሥር ይገኛሉ።
8በየመንደሩ ሥርቻ ያደፍጣል፤
ንጹሓንን በሰዋራ ስፍራ ይገድላል።
ዐይኖቹንም በምስኪኖች ላይ ያነጣጥራል።
9በደኑ ውስጥ እንዳለ አንበሳ በስውር ያደባል፤
ረዳት የሌለውን ለመያዝ ያሸምቃል፤
ድኻውንም አፈፍ አድርጎ በወጥመዱ ይጐትታል።
10ምስኪኑም ይደቅቃል፤ ዐንገቱን ይደፋል፤
ያልታደለውም በክንዱ ሥር ይወድቃል።
11በልቡም፣ “እግዚአብሔር ረስቷል፤
ፊቱን ሸፍኗል፤ ፈጽሞም አያይም”
ይላል።

12 እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፤ አምላክ ሆይ፤ ክንድህን አንሣ፤
ረዳት የሌላቸውንም አትርሳ።
13ክፉ ሰው በእግዚአብሔር ላይ ለምን ክፉ ይናገራል?
በልቡስ፣ “ስለ ሥራዬ አይጠይቀኝም”
ለምን ይላል?
14አንተ ግን መከራንና ሐዘንን ታያለህ፤
በእጅህም ዋጋ ለመክፈል ትመለከታለህ፤
ምስኪኑም ራሱን በአንተ ላይ ይጥላል፤
ለድኻ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።
15የክፉውንና የበደለኛውን ክንድ ስበር፤
የእጁንም ስጠው፤
ምንም እስከማይገኝ ድረስ።

16 እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው፤
ሕዝቦችም ከምድሩ ይጠፋሉ።
17 እግዚአብሔር ሆይ፤ የተገፉትን ምኞት ትሰማለህ፤
ልባቸውን ታበረታለህ፤ ጆሮህንም ወደ እነርሱ ጣል ታደርጋለህ፤
18ከዐፈር የተፈጠረ ሰው ከእንግዲህ
እንዳያስጨንቃቸው፣
አንተ ለድኻ ዐደጉና ለተገፋው ትሟገታለህ።
Copyright information for AmhNASV